ዘነበ ታምራት ገብረ ማርያም
ቀን ጠባ ቀን መሸ ለኛ ምን ፋይዳ አለው
መጎተት መታሰር የቀን ውሏችን ነው
መቀጥቀጥ መደብደብ ቁርስ ምሳችን ነው
ካለፍርድ መረሸን የበየኑብን ነው
አቤቱታ ሰሚ ኧረ የት ነው ያለው?
የዓለም ማሕበሩ ኒውዮርክ ላይ ያለው
የተመድ የሚሉት ሺባ ድርጅት ነው?
የዓለም ፍርድ ቤቱ ዤኔቫ ላይ ያለው?
ወይንስ ዋሽንግተን ኸዋይት ሃውስ ነው?
አቤት የሚባለው
ለዓለም ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ነው?
ወይንስ ለአምኔስቲ የመብት ተሟጋች ነው?
አቤቱታ ሰሚ ተው በቃ የሚለው
ሕዝብን ከአምባ ገነን ቀጥቃጭ የሚያድነው
የትኛው ማሕበር የትኛው ተቋም ነው?
አምባ ገነን ከቶ በማን ነው እሚዳኘው?
በጴጥሮስ ጋሊ ነው?
ወይ በአሜሪካኑ በቢል ክሊንተን ነው?
እየተቀጠቀጥን በአምባገነን በትር
ሰለባ እየሆንን ለወያኔ አሩር
የፍርድ ያለህ እያልን የምንጮኽ ዘወትር
ጠፍቶን አኮ አይደለም አፀፋ መሰንዘር
ነገር ግን ታጋዮች እመዐሕድ ውስጥ ያለን
ፍጹም ንጹህ ዜጎች በሰላም የምናምን
ለመስዋእት የቀረብን የአብርሃም በጎች ነን
የምንገደለው በጨለማ በቀን
ደማችን የሚፈስ ለአገር ለወገን
ሺበሺ እያለቅነ ወደኋላ የማንል
አጥተነው አይደለም የጫካውን ትግል
ነገር ግን ነን እኛ መተኪያ የሌለን
የቁርጥ ቀን ልጆች ኸመዐሕድ ያለን
የአገር ፍቅር እሳት የሚያንገበግበን
ትውልደ አማራ ፤ የሰላም አርበኞች ፤ የአብርሃም በጎች ነን!
ሆኖም ችለን፤ ችለን፤
እምብየው ካላችሁ መላ እንመታለን፤
ካችአምና ያኘክነውን ዘንድሮ እንውጣለን፤
በገድሎ መጣሉ እንበልጣለን እንጂ መች እኛ እናንሳለን።
በአብሮ መኖር አምነን ዛሬም እንደ ጥንቱ
ነው ብለን ነው እንጂ የሰላም ሰብሃቱ
አቤት የምንለው በየአደባባዩ፤ በየፍርድ ቤቱ
መች ጠፋን ከቶውን ለእኛ ወንድነቱ!
ነገር ግን አያልቅም የአማራ ትግስቱ
እኛ በትእግስት መላ እናፈላልግ እናንት ጮቤ ምቱ
ተመድ ነው ዋይት ሃውዝ የሚቀርብ ሙግቱ?
ክስ የሚቀርብበት የት ነው ፍርድ ቤቱ?
ኸዋይት ሃውዝ ነው ዋና ጽሕፈት ቤቱ?
ወይንስ ከስተጀርባው ኸመኖሪያ ቤቱ?
ኸፕሬዘዳንቱ?
የትነው መሟገቻው እንዴት ነው ሥርአቱ?
የት ነው አቤት የሚል ሕዝብ ሲደፈር መብቱ?
ወያኔ ሰው ሲፈጅ ዘር እየቆጠረ በአያቱ በአባቱ።
ዓለም አቀፍ ያሉት የታል ፍርድ ቤቱ?
ፍርድ ቤት ከሌለ ካልተሰማ እውነቱ
ጆሮ ዳባ ካለ ተሰምቶ ጩኽቱ
የተመድ ሽምድምድ አቅም የሌለው ነው፤
ጋሊ ድሮውንም ውሃ ውሃ የ የሚል የጥንት ጠላቴ ነው፤
የተመድ በውስጡ ሰው የለው!ሰው የለው!
ዋይት ሃውዝ ድንጋይ ነው!
ክሊንተንም ሰምቶ ሰማሁ የማይል ነው
ዋይት ሃውሰ በውስጡ ሰው የለው ሰው የለው!
እኔ አቤት አልልም ለቢል ክሊንተን
አልለማመጥም ግብጻዊ ጋሊን
የተመድ ለአገሬ መፍትሄም አይሆን
ያገሬ ልጅ ተነስ እወቀው እቅጩን
አይቼዋለሁኝ የአፍሪካ የፈረንጁን
ያለኸው አንተነህ ትጥክህን አጥብቅ
ለነጻነታችን እንተናነቅ
ያገር ልጅ ቤልጅጌ ያገር ልጅ ምንሽር፤
ያገር ልጅ ጓንዶዬ አንጀቴን የሚያሽር፤
ያገር ልጅ ጠብመንጃ የአገር ልጅ አልቤን፤
ጠፍረህ አምጣልኝ አስረህ እጅ እጁን፤
አቶስታሹንና ቀጥቃጭ ቀጥቃጩን።
No comments:
Post a Comment