ግማሽ ቀልድ አላውቅም!
ሞት እንደሆን ልሙት በሰኮንድ መቶኛ
ዕንቅልፍ እንደ ሬሳ ዘላለም ልተኛ።
መንገድ ስጡኝ ሰፊ፤
ጉዞ ከጽንፍ አጽናፍ፤
ፍጥነት`እንደ ብርሃን ዓለማትን ልለፍ።
ፀሐይ ልሁን ፀሐይ፤
እንደ ፅርሐ አርያም ሁሉንም የሚያሳይ።
እሳተ ገሞራ አመድ እረመጡን፤
ጎርፍ የሳት ጎርፍ ልሁን።
ክሲኦል ሚሊዮን ቢሊዮን ልቃጠል።
ከገሃነመ እሳት ሚሊዮን ነበልባል።
መንገድ ስጡኝ ሰፊ ---------------
ልሂድ በጨለማ ዐይን የማያይበት፤
ጥቁር የከሰለ በጠቆረው ጽልመት፤
በጸጥታው ቦታ ዘመን ከቆመበት።
በዘላለማዊው ባዶ ቦታ ዋሻ፤
አየር በሌለበት አድማስ መጨረሻ።
ልንሳፈፍ ልቃኘው፤
ለኔ ኮከብ ጠጠር ኳስ መጫወቻ ነው።
ሰው ነው የረቀቀ!
ክሜርኩሪ ቬነስ፤
ከጨረቃ ከማርስ።
ከፑሉቶ ኔፕቱን ኡራነስ የላቀ፤
ከጁፒተር ሳተርን ፀሐይ የደመቀ፤
ባካባቢው ሁሉ እያሸበረቀ፤
ሰው አደገ አወቀ፤
መሬት እንቁላሉን ሰበረ መጠቀ!
ሰው ዓለምን አየ!
በጨለማው ቦታ ዶቃ አንፀባራቂ፤
ውብ ሰማያዊ ኳስ ሮዝ አብረቅራቂ።
በተጣራው አየር በነጣው ደመና፤
በአረንጓዴ እጣቢ ውሃ ተሸፍና፤
ውብ ሉል ኮከብ ዓለም፤
የጠፈር ላይ ጤዛ፤
የስው ልጆች እናት የሰው ልጆች ቤዛ።
የመሬት ቁራጭ ነኝ፤
ታሪኳን የምጽፍ፤
በጥቁር ወረቀት በሰማይ ብራና፤
ስጓዝ እተዋለሁ በጠፈር ላይ ፋና።
ስሄድ እኖራለሁ --------------------
ሰማየ ሰማያት እመዘብራለሁ።
የተዘጋውን በር እበረግዳለሁ።
የሌለ እስኪፈጠር የሞተ እስኪነቃ፤
በትልቅ እርምጃ ከመሬት ጨረቃ
ከጨረቃ ኮከብ
ካንዱ ዓለም ወደ አንዱ፤
ስጓዝ እፈጥናለሁ -------
በፀሐይ ላይ ቤቴን ጎጆ እቀልሳለሁ።
ግማሽ ቀልድ አላውቅም!
ከሲኦል ሚሊዮን ቢሊዮን ልቃጠል።
ከገሃነመ እሳት ሚሊዮን ነበልባል።
መንገድ ስጡኝ ሰፊ ……………………
No comments:
Post a Comment