Wednesday, February 28, 2018

የአላጌው ሳቢሳ

የዛሬ 122 አመት በዳግማዊ ምኒሊክ ከተመራው ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት መሪዎች መካከል የአምባላጌው ጌታ ተብሎ የሚታወቀው አስደናቂው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ ይገኝበታል። እርሱ የሚኒልክ የጦር ሚኒስቴርና የማይደፈር በሕይወቱ እያለ አገሩ እንደማትደፈር ያቅ የነበር ቆራጥ ጀግና ነበር። በመሆኑም ገና ለዘመቻ ሲነሳ ንጉሠ ነገሥቱን እንዲህ ሲል ቃል አስገባ። "ጌታዬ ምኒልክ ሆይ! በጦርነቱ ስዋጋ በስተጀርባዬ ብመታ እዛው ለአሞራ ጣለኝ። ግንባሬን ተመትቼ ብወድቅ ትውልድ አገሬ አንጎለላ ቅበረኝ“ ከዛም ጀግናው ገበየሁ የአደዋውን ድል የአምባላጌን ምሽግ በመስበር ከፈተ። እዚያም የጣልያን ጦር እምሽክ አለ። በመቀጠልም በሌላ የጦርነት አውድማ የጠላት ሃይል አይሎ ወታደሮች መሽሽ ሲጀምሩ ” እናንት  የምትሽሹ ሰዎች ”እነ ገበየሁ እንዴት እየተዋጋን እንደሞትን ተናገሩ“ ብሎ ወደ ተፋፋመው ጦርነት በመግባት አያሌ የጠላት ወታደሮች እረፍርፎ ተሰዋ። እኔም ከዚህ ቀደም ”የአደዋው ድል ቀንዲል“ በሚል ርእሰ ግጥም ዘከርኩት። አልበቃ ቢለኝ ዛሬ ደግሞ " የአላጌው ሳቢሳ“ በሚል ርእሰ ደገምኩት። አንብቡት። እንኳን ደስ አለን!

የአላጌው ሳቢሳ

                                      ዘነበ ታምራት ገ/ማርያም

የንጉስ ፊታውራሪ የእላጌው ሳቢሳ

ቁርስ እበላ ብሎ በሌሊት ተነሳ

ቅንጬ አይደል ጨጨብሳ የዛሬውስ ቁርስ

የነጣ በሬ ነው የሚርመሰመስ

መሽጎ አምባላጌ አገር የሚያምስ

በጎራዴ ታርዶ ታምሶ በርሳስ

 ሳይረፍድ በጧቱ ለጥብስ የሚደርስ።

ታይቶ አይታወቅም የነጭ ጮማ ቁርስ

አምባላጌ ምሽግ ገበየሁ እስኪደርስ።

 የጦሩ ጄኔራል በተስኪያን እያሉ

ገበየሁ እያለ መች ያስቀድሳሉ

መጡ ገስገሱ እኔም እርቦኛል አስተርፍ እያሉ

ተንደርድረው ገብተው ጓዳውን ቢያዩት

ሁሉ በቁርሰ አልቁዋል ምሳ የለ እራት

ገቤ ለራሱ እንጂ አያስብ ለሰው

ያንን ሁ ሉ ጮማ ብቻውን በላው

ለምሳ እንኳ ሳይል ቁርስ አደረገው!

አምሳውን ከሁዋላ አምሳውን ከፊት

አሰብሮ ገብቶ ቁርስ ማስፈትፈት

እስቲ ተመልከቱ እንደው ለትዝብት

በማን ይፈረዳል ጄኔራል ቢያስሩት?

ራስ ደጃዝማቹ ተርበው እያሉ

ገበየሁ ጨረሰው እነሱ ምን ይብሉ?

በገዛ አውድማቸው መኳንንቱ ሁሉ

የሚበላ ጠፍቶ ጦም ዋሉ! ጦም ዋሉ!

ቁርሱን ግጥም አርጎ ሆዱን በቆዘረ

ጄኔራል ተቆጡ ገበየሁ ታሰረ።

ቢፈታ ተመክሮ ዳግም እንዳይለምደው

ጦር ከተፋፋመ ማን ነው የሚያግደው

ያው እንደበፊቱ እንደተለመደው

ከተፋፋመው ጦር እሳት ከሚነደው

በደሙ መአዛ ቀየውን አወደው።

ድል ይሰራል እንጂ ድል አያይም እርሱ

ከድሉ ሰልፍ ላይ ተናኘ ፈረሱ!

የገበየሁ ፈረስ የወግ እቃ ለብሶ 

ሲናኝ አከበረው ምኒልክ በለቅሶ

በቃ አይመጣም አለ ጀግና ተመልሶ

ይተካ ገበየሁ በባልቻ አባ ነፍሶ

ቢሆንም፤ ቢሆንም፤ ማን እንደ ገበየሁ እሳት ባፉ ጎርሶ

ይኖራል ዘላለም ምሽግ አፈራርሶ!

አለ አሉ ምኒልክ እኔም እለዋለው

የአምባላጌው ጀግና አድዋ ብመጣ እሬሳ ነው ያለው

መቀሌ ብመጣ ቋጥኝ ነው ያለው

አንጎለላ ልውረድ አጽምህን አግኝቼ እሳለማዋለው!”

ለአድዋው ጀግና ለፊታውራሪ ገበየሁ ጀግንነት መታሰቢያ

የካቲት 1 ቀን 2010 ዓም ፡ ሎስአንጀለስ ካሊፎርንያ ተጻፈ።

Wednesday, February 14, 2018

የጠፈር ባይተዋር




ገብረ ክርስቶስ ደስታ

ግማሽ ቀልድ አላውቅም
ሞት እንደሆን ልሙት በሰኮንድ መቶኛ
ዕንቅልፍ እንደ ሬሳ ዘላለም ልተኛ።
                      መንገድ ስጡኝ ሰፊ፤
ጉዞ ከጽንፍ አጽናፍ፤
ፍጥነት`እንደ ብርሃን ዓለማትን ልለፍ።
ፀሐይ ልሁን ፀሐይ፤
እንደ ፅርሐ አርያም ሁሉንም የሚያሳይ።
እሳተ ገሞራ አመድ እረመጡን፤
ጎርፍ የሳት ጎርፍ ልሁን።
ክሲኦል ሚሊዮን ቢሊዮን ልቃጠል።
ከገሃነመ እሳት ሚሊዮን ነበልባል።
መንገድ ስጡኝ ሰፊ ---------------
ልሂድ በጨለማ ዐይን የማያይበት፤
ጥቁር የከሰለ በጠቆረው ጽልመት፤
በጸጥታው ቦታ ዘመን ከቆመበት።
በዘላለማዊው ባዶ ቦታ ዋሻ፤
አየር በሌለበት አድማስ መጨረሻ።

                 ልንሳፈፍ ልቃኘው፤
ለኔ ኮከብ ጠጠር ኳስ መጫወቻ ነው።

ሰው ነው የረቀቀ
                 ክሜርኩሪ ቬነስ፤
ከጨረቃ ከማርስ።
ከፑሉቶ ኔፕቱን ኡራነስ የላቀ፤
ከጁፒተር ሳተርን  ፀሐይ የደመቀ፤
ባካባቢው ሁሉ እያሸበረቀ፤
ሰው አደገ አወቀ፤
መሬት እንቁላሉን ሰበረ መጠቀ
ሰው ዓለምን አየ
በጨለማው ቦታ ዶቃ አንፀባራቂ፤
ውብ ሰማያዊ ኳስ ሮዝ አብረቅራቂ።
በተጣራው አየር በነጣው ደመና፤
በአረንጓዴ እጣቢ ውሃ ተሸፍና፤
ውብ ሉል ኮከብ ዓለም፤
                   የጠፈር ላይ ጤዛ፤
የስው ልጆች እናት የሰው ልጆች ቤዛ።

     የመሬት ቁራጭ ነኝ፤
                ታሪኳን የምጽፍ፤
በጥቁር ወረቀት በሰማይ ብራና፤
ስጓዝ እተዋለሁ በጠፈር ላይ ፋና።
ስሄድ እኖራለሁ --------------------
ሰማየ ሰማያት እመዘብራለሁ።
የተዘጋውን በር እበረግዳለሁ።

የሌለ እስኪፈጠር የሞተ እስኪነቃ፤
በትልቅ እርምጃ ከመሬት ጨረቃ
                  ከጨረቃ ኮከብ
ካንዱ ዓለም ወደ አንዱ፤
            ስጓዝ እፈጥናለሁ -------
በፀሐይ ላይ ቤቴን ጎጆ እቀልሳለሁ።
ግማሽ ቀልድ አላውቅም
ከሲኦል ሚሊዮን ቢሊዮን ልቃጠል።
ከገሃነመ እሳት ሚሊዮን ነበልባል።
መንገድ ስጡኝ ሰፊ ……………………