Thursday, February 16, 2017

አዬ ግም ፈረንጅ

     አዬ ግም ፈረንጅ  

                        ዘነበ ታምራት

አንድ ቀን በበጋ ከአልጋ ተነስቼ
ላፍታታ አከላቴን ጅምናስቲክ ሰርቼ
ስሷን ካናቴራ ከደረቴ አጥልቄ
ቁምጣዬን ታጥቄ
የስፖርት ጫማዬን ወደዛ ወርውሬ
እንደ አቤ ቢቂላ ልሮጥ በባዶ እግሬ
ያዙኝ ልቀቁኝ አልኩ ተነሳሁ ፎክሬ
ነገር ግን ሰው ሁሉ ጫማህን አርግ አለ
አለዚያ አትወጣም አይሆንም እያለ
በሩን አንቆ ይዞ መውጫ ከለከለ
እኔ ግን ልቀቁኝ በባዶ እግሬ ነው
ሮጬ እምመጣ እያልኩ ስከራከር
ሚስቴ ሰምታ ኖሮ ብቅ ብላ ወደ በር
“የምን ጋጋታ ነው እንዲህ ያለ ሽብር”
ብላ ብታባርቅ ቶሎ ተንደርድሬ
የስፖርት ጫማዬን በእግሬ ላይ ሸንቅሬ
አልኳት “እመቤቴ እሽ ውዷ ፍቅሬ”
ሰው ሁሉ ገረመው እንዲያ ስሽቆጠቆጥ
ለካ ላስቸጋሪም እንደዛ ለሚያብጥ
አለው ልክ አስገቢ ከወገቡ የሚንጥ
እያለ ታዘበ ወይ አለማወቁ
ያልቀመሰ ሁሉ የሚስት ምላስ ብርቁ
መለስ ስትልልኝ እኔም አልኩኝ ውልቅ
አድነኝ እያልኩኝ ከሚስት ምላስ ጅራፍ ከሴት ጋር ትንቅንቅ
ከውጭ እንደወጣሁ አልኩኝ ነጠር ነጠር
ዞር ስትልልኝ ጀመርኩኝ ልወጠር
ማንን እፈራለሁ ካለ እርሷ በስተቀር
ወዲያው ተያያዝኩት ኩስ ኩስ ማለቱን
ፊቴ የሚታየውን ዳገት ቁልቁለቱን
ኩስ ኩስ ያልኩትን የአሯሯጥ ስልት
በፈረንጅ አጠራር “ጆግ” ነው የሚሉት
ጆግ ሳደርግ ጆግ ሳደርግ ጆግ ሳደርግ ስሄድ
በቬነስ ጎዳና ስሮጥ ስራመድ
ፊቴም ላብ ለበሰ ሞቅ አለ አካላቴ
ደስታ ተሰማኝ ጋለ ሰውነቴ
ዳገቱን ወጥቼ ቁልቁሉን ወርጄ አራዳው ስደርስ
ፈርጥጥ ፈርጥጥ አለኝ እንደ አጉራ ፈረስ
እሮጥ እሮጥ እያልኩ ስመታ ገርዳሳ
አየሁ መናፈሻ ለአይን የሚያሳሳ
ከታች መደብ ሆኖ አረንጓዴ ሳር
ዙሪያው በአበቦች ተከቦ የሚያምር
አልፈው አልፈው ደግሞ ዛፎች ተተክለው
ይላሉ እረፍ  እረፍ የደከመን ሰው
ይሄ መልካም ስፍራ ቀልቤን ጎትቶት
ሩጫዬን አቆምኩ አረፍ ለማለት
እንዘፍ ብል አንዴ ከአረንጓዴው ሳር
ተመኘሁ አዛ ላይ ተኝቼ ማደር
ቀይ ሮዝ ነጭ ሮዝ የአበባ እምቡጥ
ሞልቷል ከዙሪያዬ ልብ የሚመስጥ
እጅግ ተመችቶኝ አልኩኝና እሰይ
በጀርባዬ ሆኜ ቀኝ ግራውን ሳይ
የገባሁ መሰለኝ መንግስተ ሰማይ
ትንሽ እንደ ቆየሁ በዚህ አኳዃን
ይሸተኝ ጀመረ ያልሆነ ጠረን
ይሄ እንግዳ ነገር እጅጉን ገርሞኝ
እጄን ለምርመራ ዃላዬ ላኩኝ
ቀዘቀዘኝ በጣም ተነሳሁ በርግጌ
       እጄ ካካ ዝቋል
       በካካ ተረፍቋል
ጀርባዬ በሙሉ በግም ተጨማልቋል
ቱታዬን ከኋላ ዞር ብዬ ባየው
የኩቲ  ካካ ነው ያጨማላቀው
ለካ መናፈሻው እንዲያ የሚያምረው
የኩቲዎች ካካ ሰገራ ቤት ነው
ታዘብኩት ፈረንጅን ሰከን ብዬ ሳየው
ላይ ላዩ እያማረ ውስጡ ለካ ግም ነው
ፈረንጅ ላዩ ያምራል
ብሉኝ ብሉኝ ይላል
እኛን ይጠየፋል
ግን ውስጡ ይከረፋል
የአሜሪካን ግቢ ያ የኛ ክርፋት
አለው ማስጠንቀቂያ ከሩቅ የሚሸት
የፈረንጅ ክርፋት ግን የአበባ ጥቅል
ኑልኝ ኑልኝ ይላል አዙሮ ሊጥል
በመሽፋፈኑ ይበልጠናል እንጂ
አዬ ግም! አዬ ግም! አዬ ግም ፈረንጅ!
    (የሎስ አንጀለሱ ገጠመኝ 06/16/2006)



No comments:

Post a Comment