የቀድሞው የአሰብ ወደብ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ መኮንን ተክለ አብ በአደረባቸው የጥቂት ቀናት ሕመም በድንገት አረፉ። የቀብራቸው ሥነ ስርአት ቤተ ዘመዶቻቸው፤ ወዳጆቻቸውና ጓደኞቻቸው እንዲሁም በሎስ አንጀለስ ነዋሪ የሆኑ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንና ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በሆሊ ክሮስ ሴሚታሪ ማርች 19 ቀን 2017 ዓ/ም ተፈጽሟል።
በቀብር ሥርአታቸው ላይ በተነበበው የሕይወት ታሪካቸው መሰረት አቶ መኮንን ተክለ አብ እንደ እ.አ አቆጣጠር በ1953 ዓ/ም በደሴ ከተማ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን በንጉስ ሚካኤል ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በ ወ/ሮ ስሂን ት/ቤት ጨርሰው በአሰብ ወደብ አስተዳደር ዋና መ/ቤት ተቀጠሩ። በዚህ መስሪያ ቤት በማገልገል እያሉ ባሳዩት ጥረት ስኮላርሺፕ ተፈቅዶላቸው የተለያዩ የወደብ አሰተዳደር ኮርሶች በዩጎዝላቭያ በእንግሊዝና በአሜሪካን አገር በመሄድ ተካፍለዋል። እውቀታቸውን ለማዳበር ባደረጉትም ጥረት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አሜሪካን አገር ከሚገኝ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በመቀጠልም ሁለተኛ ዲግሪአቸውን እዚሁ አሜሪካ ከሚገኘው ከዴቭሪ ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል። አቶ መኮንን በስራቸው ላይ ባሳዩት ትጋትና ባስመዘገቡት ውጤት የተነሳ ከተራ ሠራተኛነትት ተነስተው የአሰብ ወደብታ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ለመሆን በቅተዋል።
አመለ ሸጋው አቶ መኮንን ተክለ አብ በ1989 ዓ/ም ከባለቤታቸው ከ/ሮ አመለወርቅ ጋር ትዳር መስርተው እስከ እለተ ሞታቸው በፍቅርና በመተሳሰብ ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ኖረዋል። ሟቹ አቶ መኮንን በነበራቸው የአገር መውደድ የተነሳ የአሰብ ወደብ በጠላት እጅ ሲወድቅ አሜሪካን አገር በስደት መኖር መርጠው ለ5 አመት ያህል በሎንግ ቢች የሎዝ አንጀለስ ወደብ ተቀጥረው ያገለገሉ ሲሆን እ አ አቆጣጠር ከ2001 ዓ/ም ጀምሮ እስከ እለተ እረፍታቸው ድረስ በጤና ዘርፍ የግል ድርጅት አቋቊመው አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበሩ።
እኝህ ታላቅ ሰው ሕይወታቸውን በሙሉ እግዚአብሔርን ፈሪ ሰውን አክባሪ ተግባብተው ነዋሪ ነበሩ። ከዚህም በላይ ለቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያን ሕብረተሰብ ፈጥነው ደራሽ እንደነበሩ ይታወቃል። ሎስ አንጀለስ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አንድ ታላቅ ሰው አጡ። የዚህ ብሎግ አዘጋጅ የሆንኩት እኔ ዘነበ ታምራትም ሊተካ የማይቻል መካሪ ጓደኛዬን አጣሁ። መኴ እግዚአብሄር ነፍስህን ይማር!አንተ ብትሞትም እኛ ስለ ሰዎች ደህንነትና ስለ አገርህ አንድነት የነበረህን ቁጭት አንረሳውም። ለውድ ባለቤትህም መጽናናቱን ቸሩ አምላክ እንዲሰጣት የዘወትር ጸሎታችን ነው።