Friday, October 28, 2016




                                                                   ሃገሬ


                 በ ገብረ ክርስቶስ ደስታ

አገሬ ውበት ነው

ለምለምና ነፋስ የሚጫወቱብት

አገሬ ቆላ ነው ደጋ ወይና ደጋ

እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ

 አገሬ ተራራ ሸለቆ ረባዳ

አገሬ ጂረት ነው ገደልና ሜዳ

ውሸት ነው በበጋ ጸሃይ አትፋጂም

ክረምቱም አይበርድም ................          

                      ለሙሉው ፎቶው ላይ ያለውን 3 ማእዘን ይጫኑ

Saturday, October 8, 2016

ኃይሉ ሻውል አረፉ






የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ባደረባቸው ሕመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው እአአ ኦክቶበር 8 ቀን 20016 ዓ/ም በ80 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ለአመታት በወያኔ እስር ቤት ሲማቅቁ የነበሩት ኃይሉ ሻውል ይቅርታ እንዲጠይቁ ተገደው ከስር የተለቀቁ ቢሆኑም በንጽህና ጉድለትና በቅዝቃዜው ከታወቀው ከቃሊቲ እስር ቤት ይዘው የወጡት በሽታ ለሞት እንዳደረሳችው ተረጋግጧል። ይህ በሽታ እያሰቃያቸው ቢሆንም ኢንጅነሩ ወያኔንም በሽታውንም እየታገሉ እስክ ምርጫ 2005/2012 ድረስ መኢአድን በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ ቆይተዋል።

የተከበሩ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በአባይ ሸለቆ ጥናት፤ በአውራጎዳና፤ በሼል ኢትዮጵያ፤ በመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ከተራ ሰራተኝነት እስከ ሥራ አስካሄያጅነት በደረሰ ደረጃ ያገለገሉ ሲሆን በደርግ ጊዜ የመንግስት እርሻ ሚንስትር በመሆን ሰርተዋል። ክቡርነታቸው የሚኒስትር ማዕረጋቸውን በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ በግል ሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ሻውል ኮንሰልት የተባለ የአማካሪ ድርጅት በማቋቋም ከአገር አቀፍ እስክ ዓለም አቀፍነት አድርሰው ስፊና ልዩ ልዩ የልማት አገልግሎት እንዲስጥ አብቅተዋል።

በ1983 ዓ/ም በትግሬ ነጻ አውጭ ግንባር የሚመራው መንግስት አማራውን በብሄራዊ ጠላትነት ፈርጆ በመላው አገሪቱ የሚገኘው አማራ ላይ እሳት ሲጭር መላው አማራ “ሞረሽ!” ተብሎ ሲጠራ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ጥሪውን ተቀብለው ወደ መላው አማራ ድርጅት በመቀላቀል በእሳት አደጋ ስራተኝነት  ሕዝብን ከጥፋት ለማዳን የተጀመረውን ርብርቦሽ በግንባር ቀደምት ነት ከሚመሩት አንዱ ለመሆን በቅተዋል። በፕሮፌሰር አስራት ወ/የስ በሚመራው በመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት  ውስጥ በምክትል  ፕሬዝዳንትነትና የውጭ ጉዳይ ሃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩት ኃይሉ ፕሮፌሰር አስራት በወያኔ እስርና ጥቃት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ በምትካቸው ተመርጠው የመአሕድ ፕሬዝዳንት ሆነዋል። በዚህም ጊዜ በቀኛዝማች ነቅአ ጥበብ ሽምድምድና የደነቆረ አመራር ፈራርሶ የነበረውን መአሕድ በማቃናት የኢንጅነር ኃይሉ አመራር አስተዋጽኦ አድርጓል። ሆኖም ፓርቲው በብሄራዊነት እንዲያገለግል ታስቦ ወደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲነት ሲቀየር መአሕድ እንደገና በእነቀኝ አዝማች ነቅአ ጥበብ እጅ በመውደቁና የባሰ ተሽመድምዶ በመቅረቱ፤ የኢንጅነር ኃይሉ አመራር ከአዲስቹ የመአሕድ አመራር ጋር ቅራኔ ከመግባት ይልቅ በመተባበር ቢሰሩ ለአማራው ሕዝብ ትልቅ ተስፋና መከታ ይሆኑ ነበር የሚሉ ወገኖች ተከስተዋል። ቢሆንም መኢአድ ለአማራው ሕዝብ መብት ከመታገል አላቆመም የሚሉ ወገኖችም አልታጡም።

በ1997  ቅንጂት ሲፈጠር መኢአድ በመዋጡ ኢንጅነር ኃይሉ የቅንጂቱ ፕሬዝዳንት ቢሆኑም መሰረታዊ ፓርቲአችን መአሕድ አይፍረስብን  በሚሉ ጥቂት የፓርቲው አባላት ጥርስ ስር መግባታቸው አልቀረም። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ከመአሕድ ቀጥሎም ከመኢአድ አክራሪ አባላት የቀረበበትን ተቃርኖ በማክሽፍ የኢንጅነሩ አመራር እየገስገስ ሄዶ በኢትዮጵያ  ታላቅ ሕዝባዊ ኃይል ሆኖ በመውጣት ወያኔን ያንቀጠቅጥ ጀመር። በአገር ውስጥ ከሱማሌ ክልል ውጭ በስተቀር  ከሞላ ጎደል በሁሉም ክልሎች የተደራጀውና በዓለም ዙሪያ በተቋቋሙት የዲያስፖራ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ይረዳ የነበረው ቅንጅት በአብዛኛው የኃይሉ አመራር ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ኃይሉ በአገር ውስጥ ከገጠር ወረዳዎች እስከ ክልል ዋና ከተሞች በመጓዝ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ሰበኩ። በአውሮፓ፤ በአሜሪካና በካናዳ በተደጋጋሚ በመዘዋወር አንድነት ኃይል መሆኑን አበክረው አሰታወቁ። የወያኔ አገዛዝም በዘር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አደገኛነቱን አስጠነቀቁ። በዚህም አመራራቸው ብቃታቸውን አረጋገጡ። በርሳቸውም አመራር ቅንጅት የ1997 ብሄራዊ ምርጫ አሸነፈ። ይሁን እንጂ ድሉ የተፈጸመው ዲሞክራሲ በሌለበት አገር በመሆኑ ውጤቱ ድል አድራጊው ወደ እሰር ቤት ድል ተነሽው ወደ ቤተ መንግስት ሆነ። ኃይሉም የዚሁ እውር ፍርድ ሰለባ ሆነው ከነወገኖቻቸውና የፖለቲካ ባልደረባዎቻቸው ጋር የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ወህኒ ወረዱ።

ከእጅግ አሰልችና እልህ አስጨራሽ ትግልና ሕዝባዊ ውትወታ በኋላ ኃይሉና ባልደረባዎቻቸው ቢፈቱም ወያኔ በመሃላቸው ገብቶ በፈጠረው ልዩነት ቅንጅት ሲፈርሰ ኃይሉ መኢአድን እንደገና አደራጅተው ለ1997ቱ አገር አቀፍ ምርጫ አቀረቡ። ይሁን እንጂ ወያኔ የምርጫ ሥነ ስርአትን በተመለከተ ድርድር ውስጥ አስገብቷቸው የምርጫ ቦርድን ያላስተካከለ ውል በመፈረማቸው ከፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው አያሌ ተቃውሞ ደረሰባቸው። ይልቁንም በዚህ ምርጫ ወያኔ መቶ በ መቶ አሸንፍያለሁ በማለት ክአንድ በስተቀር ካለምንም ሌላ ተቃዋሚ ፓርላማውን በመሙላቱ ኃይሉ እጅግ ተማረው ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አመራር ለመውጣት መወሰናቸውን በይፋ አስታወቁ። በፓርቲውም አመራር ተተኪ እስኪገኝ ቆይተው ስልጣናቸውን አስረከቡ።

ኢንጅነር ኃይሉ አልፎ አልፎ አመራራቸው በተቃርኖ (በ controversy)የታጀበ ቢሆንም በታታሪነታቸው፤ በግልጽነታቸውና በደፋርነታቸው የታወቁ መሪ ነበሩ። ለአገራቸው ያበረከቱት ወደር የሌለው  አገልግሎትም ስመ ጥር ኢትዮጵያዊ አድርጓቸዋል። ጥርሱን ካገጠጠ የትግራይ ወያኔ አምባገነን ጋር ያደረጉት ትግል በታሪክ ለትውልድ ሲተላፍ ሕያው ሆኖ ይኖራል። ደወል ለቤተሰቦቻቸው፤ ለወዳጆቻቸውና ለፓርቲያቸው መጽናናትን ትመኛለች።